53ኛው የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከነገው ዛፍ ፕሮጀክትና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ መርሐግብሮች ተከብሯል።
በዛሬው ዕለት ከኮሌጁ ግቢ በመነሳት መዳረሻውን ጉለሌ እጽዋት ማዕከል ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር ማራኪ የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን ይህ ጉዞ የአካባቢ ጥበቃን መልዕክት በስፋት ከማስተላለፍ ባለፈ የተሳታፊዎችን የአካል ጤንነት ለመጠበቅ እና ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ ነበረው።
ከእግር ጉዞው ጎን ለጎን የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራም የተከናወነ ሲሆን በመርሐግብሩ ላይ ስለ ጉዞው ዓላማና የቀጣይ ስራ እንቅስቃሴ በዝግጅቱ አስተባባሪዎችና በባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡በማብራሪያውም የዚህ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ "ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በአግባቡ በመንከባከብ ዛፍ ሆነው ማየት፣ የአካባቢን የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ እና ከዕፅዋት የሚገኙትን ልዩ ልዩ ገጸ-በረከቶች በአግባቡ መጠቀም ነው" ሲሉ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ኮሌጁ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ተመሳሳይ የአካባቢ ጥበቃ የእግር ጉዞዎች እንደሚኖሩ፣ የችግኝ ተከላ መርሐግብሮች በስፋት እንደሚካሄዱ እና በተለይም ችግኞችን ከተተከሉ በኋላ የቅርብ ክትትልና እንክብካቤ የማድረጉ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።
በተመሳሳይ ዜና በዓሉን ምክኒያት በማድረግ በትናንትናው ዕለት የአካባቢ ጥበቃን ፅንሰ ሀሳብ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን መነሻ ያደረገ የፓናል ውይይት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በኮሌጁ ተካሂዷል። 
.